አምራቾች እኩል እንታይ ሲሉ ምሬታቸውን ገለጹ

  0
  2173

  ባሳለፍነው ረቡዕ የአርበኞች ቀን በተከበረበት እለት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተጠራ እና በሸራተን አዲስ በተካሄደ ዝግ መድረክ አምራች ባለሃብቶች መንግስት ላይ ከፍተኛ ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን ቦታው ከነበሩ ምንጮች ካፒታል መረጃ አግኝታለች፡፡

  በመድረኩ የተሳተፉ እና ስማቸው ጎልተው የሚጠሩ ድርጅቶች ባለቤቶች እና ተወካዮች መንግስት የአገር ውስጥ አምራች ዘርፉን ፈጽሞ ዘንግቶታል ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

  እንደምንጮች ገለጻ በከፍታኛ የጭብጨባ አጀብ ጭምር የተሰጡት ከፍተኛ የቅሬታ አስተያየቶች መንግስት በተመሳሳይ ዘርፍ የሚገኙ የውጭ ባለሃብቶችን በተለያየ ሁኔታ እየደገፈ የአገር ውስጥ ባለሃብቱን ከጨዋታ እያስወጣ ነው ሲሉ ተደምጧል፡፡

  ‘አምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ ተዋንያን እና የመንግስት የምክክር መድረክ’ በሚል ርዕስ በተጠራው ስብሰባ ባለሃብቶች የመሬት አቅርቦት ከቀደመው ብልሹ መንገድ መሻሻል እንዳለበት መስክረው መንግስትን አመስግነዋል፡፡

  ሆኖም ከውጭ ምንዛሬ፣ ከግብር፣ ከተጋነነ ደረሰኝ (ኦቨር ኢንቮይስ)፣ ከደረሰኝ አሰጣጥ፣  እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር የውጭ ባለሃብቶች ያልተገባ ድጋፍ እና ከህግ ያፈነገጠ እንቅስቃሴ ውስጥ እየሆኑ እርምጃ ያለመውሰድ ሁኔታ አለ ይህም እኛን ከውድድር እያስወጣን ነው ሲሉ ትልልቅ ባለሃብቶች ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

  የውጭ ኩባንያዎች ካለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈጽሙ ጠያቂ የለባቸውም፣ ገቢ እወቃን በተጋነነ ደረሰኝ (ኦቨር ኢንቮይስ) እያስገቡ የውጭ ምንዛሬ ያሸሻሉ፣ የምርት ወጪያቸው በሃሰት እንዲንር ያረጋሉ በአንፃሩ የአገር ውስጥ ባለሃብት በትክክለኛው አለም አቀፍ ዋጋ ያስገባው እቃ ደረሰኝ ከውጭዎቹ ጋር በማነጻፀር እንደ አጭበርባሪ እየተቆጠረ ቅጣት እየተጣለበት ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አብራርተዋል፡፡

  በዱቤ ሽያጭ/ሰፕላየርስ ክሬዲት የውጭ ባለሃብት እንደልብ የውጭ ምንዛሬ ያገኛል ይሄ ግን በተመሳሳይ ዘርፍ ላለ የአገር ውስጥ ባለሃብት ተነፍጓል በዚህም ስራ መስራት እና መወዳደር አልቻልንም መባሉ ታቋል፡፡

  አንድ ተሳታፊ ማን በአግባቡ ይሰራል የሚለውን ለማየት የምንከፍለው አመታዊ የትርፍ ግብር ከውጭዎቹ ባለሃብቶች ጋር ይነፃፀር ያሉም ባለሃብቶች ነበሩ፡፡

  በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለካፒታል የሰጡ አንድ ባለሃብት ሃሳቡን ደግፈው ማን ተገቢውን ይከፍላል ባግባቡም ይሰራል የሚለውን ለማረጋገጥ ገቢዎች ሚኒስቴር በያመቱ ከፍተኛ ግብር ከፋይ እያለ የሚሸልማቸውን ድርጅቶች ዝርዝር መመልከት ነው ብለዋል፡፡ የውጭ አምራች በዚህ ዝርዘር እጅግ ውስን ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

  በመድረኩ የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስትር፣ መላኩ አለበል፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ደበሌ ቃበታ፣ ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር አባይ እንዲሁም ሌሎች ሃላፊዎች እንደነበሩ ታውቋል፡፡

  ሆኖም መድረኩ ለሚዲያዎች ክፍት አልነበረም ወይም ሚዲያዎች አልታደሙም ሲሉ ምንጮች ተናግረዋል፡፡